ዩናይትድ ስቴትስ በኢትዮጵያ ጉዳይ ሥጋቷን ገለፀች | VOA

የዩናይትድ ስቴትስ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው የውጥረት ሁኔታ ሥጋት ያደረባት መሆኑን የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቷ ቃል አቀባይ ጃን ኪርቢ ዛሬ ከአሜሪካ ድምፅ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት መልስ አስታውቀዋል፡፡

23572344-a31b-4091-af6c-16632f30951a_w987_r1_s

ጃን ኪርቢ – የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ

ዋሺንግተን ዲ.ሲ. —
የዩናይትድ ስቴትስ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው የውጥረት ሁኔታ ሥጋት ያደረባት መሆኑን የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቷ ቃል አቀባይ ጃን ኪርቢ ዛሬ ከአሜሪካ ድምፅ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት መልስ አስታውቀዋል፡፡

በኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች ላነሷቸው የመሬት መብትና የምርጫ ሕግን ማሻሻያ የመሳሰሉ ብሦቶች መልስ ለመስጠት መንግሥት ቃል መግባቱን ፕሬዚዳንት ሙላቱ መስከረም 20 ለፓርላማው ያደረጉትን ንግግር መንግሥታቸው እንዳጤነው ቃል አቀባዩ ገልፀው የኢትዮጵያ መንግሥት ያቀረባቸውን ሃሣቦች ተግባራዊ ለማድረግ በቁርጠኝነት እንዲንቀሣቀስ እንደሚያበረታታ አመልክተዋል፡፡

ኪርቢ በማከልም የኢትዮጵያ መንግሥት ባለፈው ሣምንት መጨረሻ ላይ የደነገገውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፤ በተለይም ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሰዎችን መያዝን፣ ነፃ ሃሣብን መገደብን፣ ሕዝባዊ ስብሰባዎችን ማገድን እና የሰዓት ዕላፊ ገደብ መጣልን የመሳሰሉ የአስቸኳይ ጊዜ እርምጃዎቹን ተግባራዊ ለማድረግ የሚፈልግበትን ሁኔታ ግልፅ እንዲያደርግ መንግሥታቸው እንደሚፈልግም አስረድተዋል፡፡

“እነዚህ እርምጃዎች ሥርዓትን ለመመለስ የታሰቡ ቢሆኑ እንኳ – አሉ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ ጃን ኪርቢ – ነፃ ድምፆችን ማፈንና በኢትዮጵያዊያን መብቶች ውስጥ እራስን የሚጎዳ ጣልቃ ገብነት ማድረግ ለብሦቶቹ መፍትኄ ከማግኘት ይልቅ ሁኔታዎችን የሚያባብሱ ነው የሚሆኑት፡፡”
ምንጭ:-VOA