አነጋጋሪው የአርቲስት ሜሮን ጌትነት ግጥም

“ሀገሬ”
ልክ ነበርክ አንተ
እዚህ ለፍተህ ስትኖር ባገርህ አፈር ላይ
‘አባን ከና’ የሚል ያንተን ልፋት የሚያይ
አንዳችም ሰው የለም ህዝቡ ውጭ አምልኳል
ልቡ ተንበርክኳል
ላገር ስታነባ በጥቅም ይለካል
በነጻ ያላበህ በዶራል ይተካል
አሁን በቀደም ለት
ለቤታችን ምርጊት ያቦካናት ጭቃ
ብሎኬት ለማቆም ቦታው ተፈልጎ ተጣለች
ተዝቃ
ተመስገን ማለት ነው ቀርቶ መማረሩ
ስንዝር መቀበሪያም ካልጠፋ ባገሩ
ተመስገን ነው ጥሩ
ለኑሮማ ሚሆን መሬት ማን አሲዞን
ቤታችን ወደ ላይ ቢቀርበን እግዜሩ
ወደላይ ነው ጥሩ
ወደ ላይ ወደ ላይ ወደላይ አሻቅቦ
አ ንደኛው ባንዱላይ ኑሮውን ደርቦ
……ህ…….. ም……….

እግዚያር ቀረበ ጸሎትህ ተሰማ
ባለ – ቤት ልትሆን ነው እዚሁ ከተማ
እሰይ፥ እሰይ እሰይ የምስራች ለነዋሪው ሁሉ
ሀገር ለወደደ ከነምናምኑ
ለደሃው የሆነ ደርሶ ለተገፋ
ፎቅ ቤት በያይነቱ መጣ በወረፋ
ሲባል ጆሮህ ሰምቶ
ከጸሎትህ ጋራ እጣ ፈንታህ ገብቶ
የጣ ቁጥር ይዘህ አመታት ቆይቶ
ቆይቶ ቆይቶ ቆይቶ ቆይቶ….ቆ…ይ… ቶ!
ቅድሚያ ይሰጥሃል ስትከፍል መቶ
እንኳን መቶ ቀርቶ የለህም ሰላሳ
በቃ እድልህን ጠብቅ
የሚያለማ መጥቶ ሰፈሩ እስኪነሳ
……እናልህ ወዳጄ……..
ከዚህ ሁሉ ፍዳ ከዚህ ሁሉ ጣጣ
ምን አለበት አሁን ደርሰህ ብትመጣ
ምን ያደርግልሃል? ምን ያደርግልሃል? መሆን
ያገር ዜጋ
ሞልቷል ትርፍ መሬት ክፍቱን የሚያዛጋ
ነጻ ሚሰጥህ ግን በሰው ሃገር ለፍተህ ላገኘኸው
ጸጋ
እንዲሆንህ ዋጋ
……ህ…….. ም……….
ጠብታ ውሃ ነው ድንጋይ የሚበሳ
እንጩህ ዝምብለን ህዝብ እስከሚነቃ ሀገር
እስኪነሳ
ብዬህ ነበር ያኔ አለማወቅ ደጉ
ለካስ ወርቁን ትቶ ለመዳብ ነው ጉጉ
ሀገር መሀል ሆነህ ሀገር መሀል ሆነህ
ለሀገር ስትጮህ፥የለም የሚያዳምጥ
ማዶ ስትሆን ነው የሹክሹክታህ ጉልበት ሀገር
የሚለውጥ
ብትስቅ ብታለቅስ ሰዉ በወረፋ ሊያይህ የሚጋፋ
ዘፈንህ የሚያምር እስክሳህ የሚደምቅ
ካገር ስትወጣ ነው ጥበብህ የሚረቅ
እድሜህን ቀርጥፈህ ብቶን ባለ ድግሪ
ማስትሬት ዶክትሬት ብትደክም ብትለፋ
እውነቱን ልንገርህ በሃገሬ ሂሳብ
ከውጪ የመጣ የሶስት ወር ኮርስ ነው ሚዛኑን
ሚደፋ
…..ይሄወልህ ወዳጄ…….
ያገሬ ጎበዛት ህዝብ የምንላቸው
ያለኛ ጨውነት ጥፍጥናም የላቸው
ብለን ያንልላቸው
ባንተ ካገር መኖር ጉዳይም የላቸው
ምን ታሪክ ቢሰራ ነብይ በሀገሩ መቼ ይከበራል
ተረት እያወሩ
ጸበል ጓሮ አግኝተው ቁርበት ነከሩበት
በል እኔን አትስማኝ አንተ እወቅበት
……አሁን ሌላውን ተው……..
ቀበሌ ሄደሃል ገጥሞህ አንዳች ጉዳይ
በሀገር ነዋሪ መሆንህ እንዲታይ
ይታወቅልህ ዘንድ የነዋሪ መግለጫ
ስጡኝ ብትላቸው
ሰው የለውም ቢሮው ባዶ መቀመጫ
አ ሁን ለሻይ ወጡ ጠጥተው እስኪመጡ
አንድ ሁለት ሶስት ሰአት አርፈው ይቀመጡ
ነገ ደግሞ የሉም ስለሚደክማቸው
እረፍት ላይ ናቸው
የሆነ ቀን ታመው ሌላ ቀን ረስተው
ወጡ ሳይፈርሙ ስብሰባ ላይ ናቸው
ስራ እያስቀደሙ
ስራ እያስቀደሙ፥ ምንድን ነው ስራቸው?
ዛሬም ከስብሰባ ነገም ካለቃ ጋር
የሚያጣጥዳቸው
ያን ጊዜ ለምርጫ ቅስቀሳ ሲዞሩ
ያንተን መታወቂያ ባግባቡ ሊሰሩ
ነበረ ዲስኩሩ፣እሳቸው ግን የሉም
ባዶ ነው ወንበሩ
…….ህ……. .ም………
ተዋቸው ተዋቸው ልንገርህ
ብሄድ ነው የሚያዋጣ
አለህ የሚልህ ከሌለ ምናል ካገር ብትወጣ
አንዱ ሀገር ሶስት አመት ኖረህ
ጸጉርህን ለውጠህ ብትመጣ
ቀድሞም ችግር አይኖርህ
የማን አይን አየህ በክፉ
አንዳችም እንዳትጉላላ ሊያውም ተክነው
በዘርፉ
እንደ ሄድክበት ሃገር እረፍትም የሌላቸው
ያንተን ችግር አዳማጭ ክቡር ሚንስትር
ናቸው
ምን እንሰይምልህ በየ አደባባዩ
የሚመጡት ልጆች ያንተን ግብር እንዲያዩ
የሚባል ዘመቻ ያለው ላንተ ብቻ
……….ህ…. …ም………..
ሽማግሌ ልከህ የከለከሉህን ቆንጆዋን ኮረዳ
በፈለከው ሰአት ስበህ የምትወስደው ከትዬው
ጓዳ
በህጻን ባዋቂው እንዲያ ምትወደድ
ብትርቅ አይደልም ወይ ካገር ብት ሰ ደድ!
…….ህ……. ..ም………..
ታዘብኩት እኔኑ
ታዘብኩት እኔኑ አፈርኩኝ በራሴ
ያን የመሰለ ሃሳብ እንዲያ ማራከሴ
እንኳን በምድራዊው ባለማዊው መድረክ
ለነብስህ ልታድር ልትታረቅ ካምላክ
የላብህን ቋጥረህ ለግዚያር ስጦታ
አስራት ልታወጣ መቀነት ብትፈታ
ካንተ አንድ መቶብር
ያምስት ዶላር ጥሪ ይደምቃል እልልታ
…….ህ……. ..ም………..
ምን ያደርግልሃል? ምንያደርግልሃል?
ምስጋናቢስ ቄዬ ውለታ ቢስ ሀገር
ለሄደ እየኖረ ያለን ለሚያባርር
ምን ያደርግልሃል? ምን ያደርግልሃል?
ምስጋናቢስ ቄዬ ውለታ ቢስ ሀገር
ለሄደ እየኖረ ያለን ለሚያባርር
……አይ….እኔ. …..
ጥበበኛ ሲጎል ከያኒ ሲታጣ
ሀገር ነው የሚጎል ቄዬ ነው ሚቀጣ
ባንዲራ ነው ሚፈዝ መዝሙር ቅጥ የሚያጣ
ብዬህ ነበር ያኔ ካገር እንዳትወጣ
አገር፣አድባር የለም ጥበበኛም ጎሏል
ዋርካ ጥላ አይሆንም ሞገስ ክብሩን ጥሏል
የምን ደግሞ ዋርካ
ደግሞ የምን ዋርካ? በደና መጥረቢያ ወገቡ
ላይ ሰብሮ
መሬቱን ለልማት ግንዱን ለቤት ማግሮ
ለለውጥ መገስገስ ከተማ አሰማምሮ
ምን ያደርጋል እውቀት አስተሳሰብ ዜሮ!
በድንጋይ ላይ ድንጋይ በህንጻ ላይ ህንጻ
ፋሽኑ ዘንድሮ
ዋሽንግተን ክትፎ ስኩል ኦፍ ፕላኔት
ጀነሬሽን ቢውቲ ፍሪደም ዳቦ ቤት
የጎንደር እስክታ በክለብ አትላንታ
…..ህ……ም.. …
ይሄ ነው ትውልድህ አንዳችም ማያተርፍ
ያንተን ባገር መኖር ከቁጥር የማይጥፍ
ስለዚህ…. ስለዚህ……. አጠፍኩት
አትሂድ ያልኩትን ሽሬዋለሁ ዛሬ
ይልቅ ስቴድ ጥራኝ ልሻገር አብሬ
መቼም ያሳ ዝላይ መልሶ ከውሃው ነው
እመጣለሁ ዞሬ፤ስሜን ቀያይሬ
መቼም ያሳ ዝላይ መልሶ ከውሃው ነው
እመጣለሁ ዞሬ፤ስሜን ቀያይሬ
ያኔ ይቀበለኛል ፍቅር ያጠግበኛል
ህዝቤ… ሀገሬ…. ክብሬ
መቼም ያሳ ዝላይ መልሶ ከውሃው ነው
እመጣለሁ ዞሬ፤ስሜን ቀያይሬ
ያኔ ይቀበለኛል ፍቅር ያጠግበኛል
ህዝቤ… ሀገሬ….. ክ.ብ.ሬ